ሴፕተምበር 28፣ የማወቅ መብት መታሰቢያ ቀን

 

ሴፕተምበር 28፣ 2017

ሴፕተምበር 28፣ የማወቅ መብት መታሰቢያ ቀን

የማወቅ መብት፣ ሰብአዊ መብት ነው።

 

 SOCEPP-CAN Editorial

የመረጃ ማግኘት ነፃነትን በተመለከተ የተሰባሰቡ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ከሴፕተምበር 26 – 28 2002 (እአአ) በቡልጋሪያ ዋና ከተማ ሶፍያ ላይ ያካሄዱትን ስብሰባቸውን ሲጨርሱ በየዓመቱ ሴፕተምበር 28ትን “የማወቅ መብት መታሰቢያ ቀን” (The Right To Know Day) ሆኖ እንዲከበር ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ ይህን ውሳኔ የወሰኑት ከ15 አገሮች የመጡ የመብት ታጋዮች ሲሆኑ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በያመቱ ዕለቱ የሚታሰብባቸው ሀገሮች ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው።

ይህ ቀን በሀገራችን በኢትዮጵያም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በይፋና ያለ አንዳች መሸማቀቅ የሚያከብሩበት ቀን እንደሚመጣ እንታገላለን፣ ቀኑ እሩቅ እደማይሆንም ተስፋ እናደርጋለን።

በሀገራችን በኢትዮጵያ ይህ መብት ሙሉ በሙሉ የተጨፈለቀ በመሆኑ መንግስት ከህግ በላይ ነው.። ተጠያቂነት የሚባል ነገር አይታወቅም፣ ጥፋት የፈጸሙ ባለስልጣኖች አላንዳች ተጠያቂነት በስህተት ላይ ስህተት፣ በጥፋት ላይ ጥፋት እየሰሩ እንዲቀጥሉ ይደረጋል። የፀጥታ ሀይሎቹ በተከታታይ ሰው ሲያሰቃዩ ሲገድሉ ማንም አይጠይቃቸውም ለፍርድም አይቀርቡም፣ ። ባጭሩ ተጠያቂነት የለም፣ መንግስት ከተጠያቂነት በላይ ነው ማለት ነው።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር በይፋ በቴሌቪዥን ቀርበው ሀገራችን ውስጥ የግል እሰር ቤቶች አሉ ብለው በመናገር ህዝባችን ምን ያህል ሰብአዊ መብቱ አየተረገጠ እንደሆነ በተናገሩባት ሀገር የዜጎች የማወቅ መብት የታፈነ በመሆኑ እነዚህ የግል እስር ቤቶች የት እንደሆኑ፣ የሚያንቀሳቅሱዋቸውስ አነማን እንደሆኑ አሁንም መንግስት ለህዝብ ይፋ አላደረገም። ግልጰነት ስለሌለና የማወቅ መብት ስለታፈነም የተባሉት እስር ቤቶች መዘጋት አለመዘጋታቸው፤ ወንጀሉን የሰሩት ግለሰቦችም ይሁኑ ቡድኖች ለፍርድ መቅረብ አለመቅረባቸው የሚታወቅ ነገር የለም።

የማወቅ መብት የተነፈገባት ሀገራችን ውስጥ እጅግ ብዙ ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ የት እንደገቡ አይታወቅም፡፣ ስለተሰወረ ሰው ጠይቆ መልስ ማግኘትም አይቻልም። ራሱ ለመጠየቅ መሞከርም ወንጀል ነው፡።

የማወቅ መብት በታፈነበት መንግስት ስር የምትገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ የሀገሪቱን ሀብት የሚመዘብሩ ባለስልጣኖች ጉዳይ ተሸፋፍኖ ይታለፋል። ለህወሀት ኢህአዴግ ታማኝ እስከሆኑ ድረስ ተጠያቂነት የሚባል ነገር ቦታ የለውም፡ ባለስልጣናቱ ተጠያቂ የሚሆኑት ከስርአቱ ጋር ግጭት ውስጥ ሲገቡ ብቻ ነው።

የማወቅ መብት ሰብአዊ መብት ነው። የማወቅ መብት አንድ ዜጋ መንግስት ስለሚሰራቸው የተለያዩ ጉዳዮች የማወቅ ሙሉ መብቱ ሊረጋገጥለት እንደሚገባ ፣ መንግስትም የሚሰራውን ስራ ለዜጎች በማሳወቅ ግልፅና ተጠያቂ እንዲሆን የሚያግዝ መሳሪያ ነው። ዜጎች የራሳቸውን መብት ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን መንግስትንም ተጠያቂ የሚያደርጉበት መሳሪያ ነው።

የማወቅ መብት ሲረጋገጥ ዜጎች መንግስት የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች፣ በምን መሰረት ላይ ተመርኩዞ እንደሆነ ለማረጋገጥ እድል ይሰጣቸዋል። መንግስትንም ለሚወስደው እርምጃ ሁሉ ተጠያቂ ያደርገዋል። የሀገሪቱን ንብረት ማባከንና ምዝበራ እንዳይኖር ዜጎች በመንግስት ላይ ቁጥጥር እንዲኖራቸው ያግዛል። በስልጣን በመባለግ፣ ከህግ ውጭ በሆነ መልክ ወዘተ መንግስት የሚወሰዳቸውን እርምጃወች እንዴትና በማን እንደተወሰኑ በትክክል በመረዳት ለሚፈፀሙ ስህተቶችም ተጠያቂ የሆነው ግለሰብ ወይም ቡድን በትክክል እንዲጠየቅ ያሰችላል።

ባጠቃላይ ይህ መብት ሲከበር ዜጎች የበላይ እንደሆኑ መንግስት ደግሞ የህዝብ ቁጥጥር እንዳለበት ፣ ተጠሪነቱም ለህዝብ እንደሆነ በትክክል ያመለክታል።የማወቅ መብትና ፣ጨምሮ የህዝባችንን ሰብአዊና ዴሞክራሲአዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ለማስከበር በሚደረገው ትግል ግቡን እንዲመታ ጥረታችን ይቀጥላል።