ያልተፈቱ የህሊና እስረኞችን በተመለከተ

ስላም ለተከበራችሁ ኢትዮጵያውን፣ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለክቡር ዶ/ር አቢይ አህመድና ለመላው አጋሮቻቸው

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እሥረኞች አንድነት ኮሚቴ (ኢፖእአኮ-ካናዳ)  በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዶ/ር አቢይ መሃመድ መሪነት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በቅርብ ሁኖ መከታተል ብቻም ሳይሆን ውጤቱም የተሳካና ዘላቂ እንዲሆን የበኩሉን ጥረት እያደረገ ያለ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ነው።

ዶ/ር አቢይ ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ  ብዙ ለውጦች ተደርገዋል። በየእስርቤቱ የሰብዓዊ ምብታቸው ተገፎ ለረዥም ጊዜ ሲንገላቱ የነበሩ የህሊና እስረኞች   መፈታት ኢፖእአኮ-ካናዳን ካስደሰቱት  ታላቅ እርምጃዎች አንዱ ነው። አሁንም ቢሆን በቀድሞ ጠቅላይሚኒስትር መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን ካሉበት ታፍነው ተወስደው የት እንደደረሱ ያልታወቁ የህሊና እስረኞችን ጉዳይ ተከታትሎ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለደጋፊዎቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ማሳወቁ  ሰብዓዊና ህጋዊም ነው ብለን እናምናለን።  ይህንንመ ተመልክቶ የሚሰጠው ምላሽ  ዜጎች ዛሬ እየተካሄደ ባለው ለውጥ ላይ ያላቸውን ዕምነት ሆነ የለውጡንም ውጤት ለመንከባከብም ሆነ ወደ ከፍተኛም ደረጃ ለማሸጋገር በሚኖራቸው ቀጣይ ተሳትፏቸው ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንደሚኖረው ዕምነታችን ነው።

ይህንን ጉዳይ በግንቦት 22 ፣ 2010 ላይ ከዚህ በታች የተመለከተውን ደብዳቤ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፊት-ገጸቸው (face book) አማካይነት መላካችን እያስታወስን ዛሬ በዚህ ድረ-ገጻችን ላይ ስንለጥፈው ሁላችንም ይህን በመመልከት የመልዕክታችን አፈጻጸሙን በጋራ እንድንከታተለው  በሚል ስሜት ነው። (ሙሉ ድብዳቤውን ከሥር ይመልከቱ)

Solidarity Committee for Ethiopian Political Prisoners (SOCEPP-Canada)
የኢትዮጵያ ፖለቲካ እሥረኞች አንድነት ኮሚቴ (ኢፖእአኮ-ካናዳ)
Email: socepp.can@humanrightsethiopia.com and socepp.can@sympatico.ca
http:// www.humanrightsethiopia.com

ለተከበሩ ዶክተር አቢይ አህመድ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአደግ ሊቀመንበር የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት
የ መልዕክት ሣጥን ቁጥር 1031 አዲስ አበባ፤

ኢትዮጵያ
pminfo@pmo.gov.et
ግንቦት 22፣ 2010

ጉዳዩ፦ ያልተፈቱ የህሊና እስረኞችን በተመለከተ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶ/ር አቢይ አህመድ፤
አስቀድመን እንኳን ደስ አለዎት ማለት እንወዳለን። መጪው የሥራ ዘመንዎ የጀመሩት የኢትዮጵያ ከፍታ ዕቅድ ተሳክቶ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አብበው፣ ኢትዮጵያ ሉዐላዊነቷ ተከብሮ፤ ዜጎችዋም በአገራቸው ላይ ያላቸው ሙሉ መብት ተረጋግጦ ሁሉም በፍቅርና በእኩልነት የሚኖሩባትን ሀገር ለመገንባት የሚያስችል መሠረት ጥለው የሚሄዱበት ዘመን እንዲሆንልዎ አጥብቀን እንመኛለን። የኢትዮጵያ ህዝብ፣ እርስዎም በተለያዩ መድረኮች ላይ ባደረጓቸው ንግግርዎችዎ አበክረው እንደገለፁት፣ አገራችን ውስጥ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የዜግነት መብቱ ተገፎ እየታሰረ፣ እየተጋዘና እየተገደለ የኖረ ህዝብ ነው። ይህም ሰው በዜግነቱ እንዳይኮራ፤ ሰው በሰውነቱ ያለው ክብርና ህጋዊነት ዋጋ እንዲያጣ ያደረገ ክስተት በመሆኑ የዜጎችን መንፈስ ሲያስጨንቅና ሲያሳስብ ቆይቷል። እኛ “የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች አንድነት ኮሚቴ” ወይም በእንግሊዚኛው ምህፃረ ቃል SOCEPP-CANADA(Solidarity Committee for Ethiopian Political Prisoners-Canada) እንባላለን። ድርጅታችን የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን የተፈጠረውም በአገራችን ውስጥ በጅምላ የሚካሄደውን የመብት ጥሰት ለመከላከል፤ በተለይም በየጊዜው ያለአግባብ ለእሥር የሚዳረጉ የህሊና እስረኞችን መብት ለመከራከር ነው። ኮሚቴው እነዚህን የመሳሰሉ ጥሰቶችን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ከሰላማዊ ሰልፎችና ታላላቅ ጉባኤዎችን ከማካሄድ እሰከ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በመፍጠርና እርምጃዎች እሰከማሰወሰድ በሚደርሱ የትግል ዜዴዎች በመጠቀም ሲታገል የቆየና አሁንም እየታገለ ያለ፤ ትርፍ ለማግኘት የማይሰራ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ነው። ክቡርነትዎ አዲሱን ስራዎን ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ የዜጎች መብት መከበርን አስመልክተው ያደረጓቸውን ንግግሮችና ያስተላለፏቸውን መልዕክቶች ሶሴፕ- ካናዳ በጥሞና እየተከታተለ ነው፡፡ አሁን በቅርቡ በፖለቲካም ጉዳይ ይሁን በሌላ ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ ታግተው የቆዩ ንፁሃን ዜጎች እንዲፈቱ መደረጉን ስናይ ደስታችን ከፍተኛ ነው፤ ምኞታችንም ከዚህ የዘለቀ ነው። በተጨማሪም ዜጎች በተለያዩ ጎረቤት አገሮች እየደረሰባቸው ያለውን እሥራትና እንግልት ለመታደግ የወሰዷቸው እርምጃዎችና ያስገኟችው ውጤቶች እጅግ አስደስተውናል። የተከበሩ ዶክተር አቢይ! ባለፉት ሁለት ውራት ውስጥ ሰለመብት፤ ሰለፍቅር፤ ስለዕርቅ፤ ስለአገር አንድነት፤ ስለብሄራዊ መግባባት ሆነ እነዲሁም ስለሚዲያ ነጻነትና ስለእስረኞች መፈታት ዘለግ፤ዘለግ ያሉ ንግግሮች ወደ ህዝብ አድርሰዋል። ህዝብም

በአመዛኙ የእርስዎ ንግግር ካለዎት የህዝብ ፍቅርና የአገር መቆርቆር የመነጨ ነው በሚል እምነት የተነገረው ሁሉ ተፈጻሚ ይሆናል ብሎ ተስፋ ሰንቆ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ታዲያ ይህን ተስፋችንን የበለጠ ዕውን ለማድረግ በሌሎች ዘርፎች ያሉ ጥያቄዎች እንዳሉ ሁነው አሁን የተጀመረው የፖለቲካ እስረኞችን የመፍታቱን ሂደት ሙሉ እንዲሆን አጥብቀን የምንጠይቀው ጉዳይ ነው። ለዚህም መነሻችን የአሁኑ መንግሥት ሥልጣን ከያዘበት ወቅት ጀምሮ አፍኖ የወሰዳቸውን የኢሕአፓ አመራር መሪዎችና አባላት (ፀጋዬ ገብረመድህን (ደብተራው)፣ይስሃቅ ደብረፅዮን፣ ስጦታው ሁሴን፣ አምሃ በለጠ፣ ሃጎስ በዛብህ፣ አበራሽ በርታና ሌሎችም) የት እንዳደራሰቸው እስካሁን አላሳወቀም። እነዚህን ኑሯቸውንና ውድ ሕይወታቸውን ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት ፣ ለህዝቧም ዕኩልነትና ነፃነት መከበር ያደረጉ ንፀሁሃን ዜጎችን መንግሥት የት እንዳደረሳቸው ማሳወቅ ግዴታው ነው ብለን እናምናለን። ሲሆን፤ ሲሆን ባልታሰሩ፤ አይደለም ለዴሞክራሲ ፈር ቀዳጅ የሆኑ የኢሕአፓ ልጆች፤ ሕግ አለ በሚባልበት አገር ማንም ዜጋ በፖለቲካ እምነቱ ባልታሰረ ነበር። ሰለዚህ መንግሥት ይህንን ጉዳይ በቂ ትኹረት ሰጥቶት ተገቢውን ምላሸ በአስቸኳይ እንዲሰጠን አጥብቀን እንጠይቃለን። የተከበሩ ዶክተር አቢይ! እስካሁን በንግግርዎ ያነሷቸው፤ ህዝቡን እግር ተወርች ቀፍድደው የያዙና አገሪቷንም ለአደጋ ያገለጡ ችግሮች መፈጠር ምክንያት የሆኑ አወጆችንና መመሪያዎችን፦ ፩ኛ፦ ጊዜያዊው አሰቸኳይ አዋጅ ፪ኛ፦ የሽብርተኛ አዋጅ ፫ኛ፦ አሁን ያለው “የተሻሻለውን” የሜዲያ አዋጅ ፬ኛ፦ አሁን ያለውን “የተሻሻለውን” የሲቪክ ማህበራት ህግ ፭ኛ፦ አሁን ያለውን የምርጫ ቦርድ ህግጋት በአስቸኳይ እንዲነሱ እንጠይቃለን። በእነዚህና ሌሎች በዚህ ውስጥ ባልተጠቀሱ አዋጆች ምክንያት ሆነ በሌሎች ከዓለም አቀፍ ህግ ውጭ በሆኑ መመሪያዎች በየእስርቤቶች ታግተው ያሉ የህሊና እስረኞች ሁሉ እንዲፈቱ በድጋሚ አጥብቀን እንጠይቃለን። ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሃገር የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሃገር ተመልሰው በህጋዊ መንገድ ሊንቀሳቀሱ የሚያሰችላቸውን መብት ባከበረ መልኩ በህጋዊ ዋስትና ላይ የተመሠረተ ጥሪ እንዲደረግላቸውና ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አስፈላጊው ድርድር እንዲደረግ እንጠይቃለን በመጨረሻም ጥያቄያችንን አክብረው ለሚሰጡን ቀና ምላሽ ያለንን አድናቆት ከወዲሁ ስንገልጽ በታላቅ ደስታ ነው። መልካም የለውጥና የነጻነት ጊዜ እንመኛለን !!!

 

አክሊሉ ወንድአፈረው
ሊቀመንበር የፖለቲካ እስረኞች አንድነት ኮሚቴ በካናዳ